Page 28 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 28
ደስታ መብራቱ
ይህ የመተካካት መርህ በሀገር በቀል እውቀቶች ውስጥ ሁነኛ ስፍራ እንዳለው
በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ፣ አብዛኞቹ ሃገር በቀል
የአስተዳደር ሥርዓቶች እጅግ በልጽገዋል ከሚባሉ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች ባልተናነሰ
6
መልኩ የመተካካት መርህን የሚከተሉ ሆነው መገኘታቸው ነው ። እነኚህ የመተካካት
ሂደቶች፣ በዘመናት ሂደት የዳበሩ የውይይት እና የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓቶችን መሰረት
በማድረግ እና የተለያዩ ትውልዶችን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት የሚከናወኑ
ናቸው።
ይህ የዕውቀት ዘርፍ ለየማህበረሰቦቹ ቀጣይነት ካበረከተው ቁልፍ ድርሻ ባሻገር
ለተለያዩ የምዕራባዊው ሳይንሶች በርካታ ጠቃሚ መነሻዎች እንደሰጠ ይታመናል።
ለምሳሌም ያህል፣ በሃገር በቀል ዕውቀት ተጠብቀው የቆዩት መድሃኒትነት ያላቸው አጽዋት
እና ባህላዊ ህክምናዎች የዘመናዊው ህክምና ሳይንስ ዋነኛ መንሻ እንደነበሩ እና አሁንም
እንደሆኑ ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ዛሬ የምዕራባዊው ዲሞክራሲ አዲስ ግኝት
ተደርጎ የምንሰበከው የሶስትዮሽ መንግስታዊ አስተዳደር ሥርዓት ኢትዮጵያን ጨምሮ
በበርካታ ሃገር በቀል የህዝብ አስተዳደር ሥርዓቶች ውስጥ የነበሩ እና አሁንም ያሉ
መሆናቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ መረጃዎች እንዳሉ ማቅረብ ይቻላል። ይህንን
7
በይበልጥ ለመረዳት፣ በኢትዮጵያ የሃገር በቀል ዕውቀቶች ጥናት ተቋም የተካሄዱ በርካታ
ጥናት ውጤቶችን መመልከት ይጠቅማል።
አሳዛኙ ክስተት፣ ምዕራባዊው ሳይንስ እና ትምህርት ለረጅም ዘመናት የዚህን
የዕውቀት ዘርፍ ታላቅ ጠቀሜታ እና አስተዋጽኦ ማሳነስ ብቻ ሳይሆን ስልታዊ
(systematic) በሆነ መልኩ እንዲቀጭጭ እና እንዲጠፋ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል።
የሃገራችን የትምህርት ሥርዓትም ሆነ የዚህ ውጤት የሆንነው ምሁራን በአብዛኛው የዚህ
ስልታዊ ጥቃት ሰለባ በመሆናችን ለሃገር በቀል ዕውቀት የምንሰጠው ትኩረት አነስተኛ
ሊሆን ችሏል። ይህም ሲባል፣ ሃገር በቀል እውቀቶች የሚጎሏቸው እና ሊስተካከሉ
የሚገባቸው አካሄዶች የሏቸውም ማለት አይደለም።
ባለፉት ጥቂት ዓስርተ ዓመታት በዓለማችን ዙሪያ እየተጠናከረ ከመጣው
ተደራራቢ ቀውሶች ጋር በተያያዘ ለሃገር በቀል ዕውቀቶች የሚሰጠው እውቅና ይበልጥ
እየተጠናከረ በመምጣት ላይ ይገኛል። ለዚህም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣
የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት የኮንሶ
ማህበረሰብ የአካባቢ ጥበቃ እና ልማት እና የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ጥሩ ማሳያ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ በርካታ የሃገር በቀል ዕውቀት መርሆዎች በሳይንሱ ዓለም በሚካሄዱ
ጥናቶች ውስጥ እየተካተቱ በመምጣት ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ፣ በበርካታ አፍሪካ
6 በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያለው በየስምንት ዓመቱ የሚካሄደው የሥልጣን ሽግግር ለዚህ አንድ
አቢይ ምሳሌ ነው።
7 ይህ ተቋም፣ የበርካታ ብሔረሰቦችን የአስተዳደር እና የዳኝነት ሥርዓቶች በዝርዝር በማጥናት
ለህትመት አብቅቷል።