Page 32 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 32
ደስታ መብራቱ
2. ፖለቲካችን በምህዳራዊ ዕይታ
በክፍል አንድ ውስጥ፣ በተቀነበበ ትንተና ላይ የተመረኮዙት አብዛኞቹ የሳይንስ
መስኮች ዛሬ በዓለም ዙሪያ እየተጠናከሩ የመጡትን ውስብስብ የማህበራዊ፣ አካባቢያዊ፣
ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን በጥልቀት ለመረዳትም ሆነ መፍትሔ ለመሻት
ያለባቸውን ጽንሰ ሃሳባዊ እና የትንተና ዘዴ ውሱንነት ለማሳየት ተሞክሯል። ይህም፣
ከ1960ዎቹ ጀምሮ እየበለጸገ ለመጣው ምህዳራዊ አስተሳሰብ ዋነኛ መሰረት እንደሆነው
እና የምህዳራዊ አስተሳሰብ የፍልስፍና እና የሳይንስ መስረቶችንም በመጠኑ ዳሠናል።
ባላፉት ዓመታት ውስጥ በርካታ ምሁራን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች እና
መፍትሔዎቻቸው ላይ የተለያዩ ጽሁፎች እና ትንተናዎች አቅርበዋል። አብዛኞቹ
ትንተናዎች የችግሮቹ ዋነኛ መነሻ የአመለካከት መሆኑን የሚያመላክቱ ቢሆንም የህመሙን
ምንጮች ካንድ ወይንም ከሌላ የፖለቲካ ድርጅት ከዚያም ከፍ ሲል ከአንድ ወይንም ከሌላ
ትውልድ ጋር ሲያያይዙት ይስተዋላሉ። በዚህ ፀሃፊ እምነት ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት
አብዛኞቹ ከሰለጠኑበት የሙያ መስክ ወይንም የፖለቲካ አመለካከት ጋር በተያያዘ
ከሚከተሉት የተቀነበበ ትንተና (reductionist analysis) ነው። በተለያየ ጥናት
እንደተረጋገጠው ከፍተኛ ውስብስብነት ላላቸው ችግሮች እንዲህ አይነቱን ትንተና
መጠቀም ከፊል እውነታን ከማሳወቅ ባሻገር መሰረታዊ መፍትሔዎችን የማመላከት
ውሱንነት ይኖረዋል። እንዲህ ዐይነቱን የትንተና ውሱንነት መሻገር የሚቻለው በምህዳራዊ
አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ትንተና በማካሄድ ብቻ ይሆናል።
ምህዳራዊ አስተሳስብ ለትንተና ከሚጠቀምባቸው ተምሳሌታዊ የተፈጥሮ
8
ክስተቶች አንደኛው በምስል ሁለት የሚታየው የበረዶ ቋጥኝ (Iceberg) ምስል ነው።
በውቅያኖስ ውስጥ የሚገኙ የበረዶ ቋጥኞች አብዛኛው አካላቸው በውሃው ተሸፍኖ
ክውሃው ጠለል በላይ የሚታየው አካላቸው እጅግ በጣም አነስተኛው ነው። ይህንን
እውነታ ባለማስተዋል፣ በርካታ የባህር ልምዳቸው አነስተኛ በሆኑ ካፒቴኖች የሚመሩ
መርከቦች እና በአካላዊ ታላቅነታቸውን አይደፈሩም ተብለው የታመኑ መርከቦች
ፍጻሜአቸው አሳዛኝ ሆኗል። ለዚህም እንደማሳያ፣ በዘመኑ ታላቅ የተባለችውን
9
የታይታኒክ አሳዛኝ ፍጻሜ ያስታውሷል። በሃገሮች ታሪክ ውስጥም፣ ታላቅነታቸውን ከላይ
ላይ በሚታዩ ሁነቶች ላይ የገነቡ የፖለቲካ ድርጅቶች እና አምባገነን መንግስታትም
በተመሳሳይ ሁኔታ ሲወድቁ እና ሲከስሙ ታይተዋል።
8 የበረዶ ቋጥኝ (Iceberg) ከዓለማችን ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ከሚገኘው የበረዶ
ግግር እየተገመሰ በመውጣት በውቅያኖስ ውስጥ የሚንሳፈፍ ከአነስተኛ ጉብታ አስክ ከፍተኛ ጋራ
የሚያክል መጠን ያለው የበረዶ አካል ነው።
9 ታያታኒክ (Titanic) እ.ኤ.አ. በ1911 በእንግሊዝ ሃገር የተሰራ በወቅቱ የዓለም ግዙፍ የመጓጓዧ
መርከብ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ1912 በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳፋሪዎችን በመያዝ የመጀመሪያውን ጉዞ
ወደ አሜሪካ ሃገር ባደረገበት ወቅት፣ ግዙፍነቱን ከባህር ወለል በታች ከከለለ የበረዶ ቋጥኝ ጋር
በመላተም ሊሰጥም ችሏል።