Page 36 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 36
ደስታ መብራቱ
የተቀነበበ ትንተና፡ በዚህ ክፍል መግቢያ ላይ ለማሳየት እንደተሞከረው፣ ያንድን
ፖለቲካ ምህዳር መሰረታዊ ችግሮች ባግባቡ ለመረዳት እና ዓይነታዊ ለውጥ ለማምጣት
ከሁነት እና ሂደቶች ባሻገር ጠልቆ በመመልከት መሰረታዊ የሆኑ መዋቅራዊ ምንጮችን
እና የአመለካከት ሞዴሎችን መመርመር ያሻል። እንዲህ ዓይነት አተናተን በተለይም
ሁነቶች እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ በሚፈጠሩበት እና ሂደቶችም በሚቀያየሩበት የሽግግር
ወቅት እጅግ አስፈላጊ ይሆናል። ባላፉት ጥቂት ዓመታት የሚወጡ የፖለቲካ ትንተናዎች
እና ጥናቶች ባብዛኛው በተናጠል ሁነቶች እና ሂደቶች ላይ በሚያተኩር የተቀነበበ ትንተና
ላይ የተመረኮዙ በመሆናቸው የፖለቲካውን ግለት ከማፋፋም ያለፈ አስተዋጽኦ ሊያረጉ
አልቻሉም። በመሆኑም በተቀነበበ ትንተና ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግሮች
ለመተንተን የተደረጉት ጥረቶች ምሉእነት የጎደላቸው ከመሆናቸውም ባሻገር ብዙዎቹ እጅግ
ተቃራኒ የሆኑ ማጠቃለያዎች እና አቋሞች እንዲወስዱ አድርጓቸዋል። በዚህ ረገድ የሃገሪቱ
ምሁራን እና የሚዲያ ሰዎች ባንድ አቅጣጫ የተቀነበበ ትንተና (linear thinking) ላይ
የተመረኮዘ ፖለቲካዊ ትንተናዎች ከመስጠት መታረም እና ዙሪያ መለስ እይታ ሊሰጥ
በሚችለው ሁለንተናዊ አስተሳሰብ ለመታነጽ ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል።
በጥቅሉ፣ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን አበይት ህመሞች እና ሌሎችንም በጥልቀት
ፈትሾ መድሃኒት መሻት የሀገሪቱን ፖለቲካ ወደበሰለ እና የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት
ለማሸጋገር የመጀመሪያው አስፈላጊ እርምጃ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሂደት ለፖለቲካ መሪዎች
ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በእውቀት እና አስተውሎት ላይ ለተመረኮዘ
ውይይት እና መግባባት የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህንንም ዘመኑ
በሚጠይቀው እውቀት ላይ ተመርኩዞ ለማካሄድ በምህዳራዊ አስተሳሰብ መመራት ከፍተኛ
እገዛ እንደሚያደርግ ይታመናል። በሚቀጥለው ክፍል ለዚህ ሂደት ከሚያግዙ መሰረታዊ
የምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች ዋና ዋናዎቹን እንመለከታለን።