Page 59 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 59
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
አነጋገር፣ ሰብዓዊነትን በምሉዕነቱ የማይቀበል ማንነት ለሌሎች ማንኛቸውም የማንነት
መብቶች መከበር የመቆም የሞራል ብቃት ሊኖረው አይችልም። መነሻ መሰረቱን
አልያዘምና።
ሁለተኛው ዓብይ ማንነት፣ ማህበራዊ ማንነት (social identity) ሲሆን ይህም
ማንነት የሰው ልጆች ታሪክ መመዝገብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያየ ማህበራዊ እድገት
ውስጥ ያለፈ ማንነት ነው። የማህበራዊ ማንነት ዋነኛ መሰረቱ ቤተሰብ እና ያደጉበት
ማህበረሰብ ሲሆን፣ የማንኛችንም ማህበራዊ ማንነት ከቤተሰብ እና ከማህበረሰብ
በሚተላለፉ የቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ትምህርት፣ ባህል፣ እና፣ ልማዳዊ ውርሶች የሚወሰን
ይሆናል። ስለዚህም፣ ማህበራዊ ማንነት ከከባቢ መንደር (neighbourhood) አንስቶ እስከ
ጎሳ፣ነገድ፣ እና የብሔረሰብ ደረጃ ሊኖረው ይችላል። በዚህ ማህበራዊ ማንነት ውስጥ፣
ከቤተሰብ እና ከመንደር ጋር የተያያዘው ማንነት ከሌሎቹ ማህበራዊ ማንነቶች የጠበቀ
ቁርኝት ይኖራቸዋል። በመሆኑም፣ ማንኛውም ሰብዓዊ ማንነትን ማእከል አድርጎ
ያልተደራጀ የብሔረሰብ ነፃ አውጪ ድርጅት በመንደርተኝነት መፈተኑ የማይቀር ይሆናል።
እንዲህ አይነቱ ፈተና፣ ባሁኑ ወቅት በሃገራችን በሚገኙም ብዙዎቹ የብሔረሰብ ድርጅቶች
19
ውስጥ የሚታይ ችግር ነው ።
ሶስተኛው አቢይ ማንነት፣ ፖለቲካዊ ማንነት (political identity) ሲሆን ይህም
ማንነት ከሃገረ-መንግሥት ምስረታ ታሪክ ጋር የተያያዘ የዜግነት ማንነት ነው። የዜግነት
ማንነት፣ ባንድ ሃገረ መንግስት ወይም ምድራዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች
በሚጋሯቸው የጋራ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ እሳቤዎች የሚቀረጽ ይሆናል። በመሆኑም፣ ዛሬ
ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አንድ ሰው ካንድ በላይ የሆነ ዜግነት ሊኖረው ይችላል።
ለምሳሌም ያህል፣ በአንዳንድ ሃገሮች ካለው የጥምር ዜግነት በተጨማሪ፣ በበርካታ ሃገራት
የመስራት እና የመኖር እድል ያገኘ ወይም ራሱን ከበርካታ ሃገራት በሚገኙ ዕውቀቶች
ያበለጸገ ሰው ራሱን ከኢትዮጵያዊነቱ ባሻገር አፍሪካዊ (Pan African) እና ዓለም አቀፋዊ
ዜጋ (Global citizen) ነኝ ብሎ ሊያምን ይችላል። እንዲህ አይነቱ የዜግነት ልህቀት
ለማንኛቸውም ማህበራዊ ማንነት ተገቢውን እውቅና እና አክብሮት የሚሰጥ ከመሆኑም
በላይ በመጀመሪያ ደረጃ ካነሳነው ስብዓዊ ማንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ይሆናል።
በመሆኑም፣ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የዜግነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
ለዘመናት በሃገራችን ሲራመድ የኖረው አሃዳዊ ሥርዓት ከፈጠረው የማንነት
ቀውስ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ቡድኖች በማህበራዊ ማንነት ላይ የተመረኮዙ የፖለቲካ
ድርጅቶች መስርተው ለመታገል መነሳታቸው እንደ ሃጢያት ሊቆጠር አይገባውም። በዚህ
ረገድ፣ አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች እና ተንታኞች በብሔር ለሚደራጁ ወገኖች የተለያዩ
19 የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር ለረጅም ዘመን በወለጋ ኦሮሞዎች በተለይም በሆሮ ጉዱሩ
ተወላጆች ተጽእኖ ስር ወድቋል ሲባል፤ የትግራይ ህዝቦች ነፃ አውጭ ግንባርም በአድዋ ተወላጆች
ተጽእኖ ስር እንደነበር መነገሩ፣ በብሔር ማንነት ላይ የተመረኮዘ የፖለቲካ ንቅናቄ በሰብዕአዊ
ማነነት እና በዜግነት አስተሳሰብ ካልተቃኘ ወደ መንደርተኝነት ለመውረዱ ማሳያ ነው።
51