Page 74 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 74

ደስታ መብራቱ


                                               27
           5.2 ኢትዮጵያ፣ ብዙ ሙፈሪያቶች ያስፈልጓታል
                  ከዚህ  በላይ  በቀረበው  ጽሁፍ፣  የወንዳዊነት  አስተሳሰብ  ጎልቶ  በሚታይበት
           የሃገራችን  ፖለቲካ  ውስጥ  ያለውን  ውስብስብ  ችግር  ለመፍታት  በሚደረገው  ጥረት
           የፖለቲካችንን ሴታዊነት ባህርይ ማጠናከር ሊኖረው የሚችለውን ጉልህ ድርሻ ለማመላከት
           ተሞክሮአል።  በተጨማሪም፣  እንደ  ምሳሌ  ሊወሰዱ  የሚችሉ  የሴታዊነት  መሰረታቸውን
           የጠበቁ ሴት አመራሮች እያየን በመሆኑ የእነርሱን አርአያነት ማበራከት እንደሚያስፈልግ
           ተወስቷል፡። በህዳር ወር 2013፣ ከነዚህ ተምሳሌታዊ ሴት አመራሮች አንዷ የሆኑት የሰላም
           ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩት የተባለው መልዕክት በመደበኛ እና ማህበራዊ
           ሚዲያው ላይ ከፍተኛ መወያያ ሆኖ  ነበር።  ባለሥልጣኖቻችን  የሚናገሩትን  ከልዩ  ልዩ
           አቅጣጫ  መመርመር  እና  ተጠያቂነትን  ማስፈን  ተገቢ  ቢሆንም፣  ሴት  አመራሮቻችንን
           ‘እንዴት  ተደርጎ’  በሚል  የወንዳዊነት  መንፈስ  ለመዳኘት  መሞከር  ሃገራዊ  ጉዳት
           የሚያስከትል ይሆናል።
                  ከሁሉም በላይ፣ ከብዙዎች በተሻለ ደረጃ ሚዛናዊ ናቸው ብዬ የምገምታቸው
           ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ተንታኞች እና ጦማሪዎችም የዚሁ ዘመቻ አካል የሚያስመስላቸው
           ሃሳብ ሲሰጡ ተሰምተዋል። ይህ አዝማሚያ፣ በቅርቡ በተለያየ መስክ  መታየት የጀመረውን
           አበረታች የሴት አመራር ተሳትፎ ሊያቀጭጭ የሚችል በመሆኑ አጠቃላይ ማህበረሰቡ
           በትኩረት  ሊመለከተው  ይገባል።  በዚህ  ክፍል፣  እነዚህ  ወገኖች  የሚያራምዱትን  ጎጂ
           አስተሳሰብ ቀደም ሲል ከቀረበው የሴታዊነት እሳቤ አስፈላጊነት ጋር በማያያዝ ለመተንተን
           ተሞክሯል።

                  በቅድሚያ ይህ ወ/ሮ ሙፈሪያት የተናገሩት እና ከየአቅጫው እንዲዘመትባቸው
           ያደረገው  ሃሳብ  ምንድን  ነው  የሚለውን  እንመልከት።  ምንም  እንኳን  ንግግራቸውን
           እንደወረደ (verbatim) የመስማት እድል ባይኖረኝም፣ በተለያዩ ሚዲያዎች እንደቀረበው
           ከሆነ  የሚከተሉት  አንኳር  ነጥቦች  ይገኙበታል።  አንደኛ፣  የፌዴራሉም  ሆነ  የክልሉ
           መንግስታት ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የህዝቡን እና የሃገሪቱን ጥቅም ማስቀደም አለባቸው።
           ሁለተኛ፣ ፖለቲከኞቻችን በሃሳብ ተለያየን ብለው አይንህን ለአፈር መባባላቸው ነውር ነው።
           ሶስተኛ፣  መርዝን  ከሚረጩ  ጥቂት  ፖለቲከኞች  ባሻገር  ህዝብ  እና  ሃገር  የሚባሉ  ታላቅ
           ጉዳዮች አሉ። አራተኛ፣ በር ዘግቶ እንኪያ ስላንቲያ ከመግጠም ይልቅ ወደ ጠረዼዛ ዙሪያ
           መጥተን መወያየት ይኖርብናል። አምስተኛ፣ ያለብንን የፖለቲካ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ
           ለመፍታት አሁንም እድሉ አለን። ነገር  ግን ይህ ዕውን እንዲሆን በሁለቱም ወገኖች ያሉ
           የፖለቲካ መሪዎች ሰከን ሊሉ ይገባል የሚሉ ነበሩ።






           27  የዚህ ክፍል አብዛኛው፣ ጥቅምት 6 ቀን 2013 በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሟል።
   69   70   71   72   73   74   75   76   77   78   79