Page 91 - ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ Final
P. 91
ምህዳራዊ አስተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ
ይህ በአብዛኛው፣ አንድን ቋንቋ ከመግባቢያ መሳሪያነት ይልቅ በመጨቆኛ
መሳሪያነት ከሚያቀርበው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ በሽታ ጋር የተያያዘ ነው። በሌላ
በኩል ግን፣ እንደ ኢትዮጵያ ባለ በርካታ ቋንቋዎች በሚነገርበት ሃገር የፌዴራሉ የስራ
ቋንቋ ባንድ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር መጠበቅም አይቻልም። ስለሆነም፣ በበርካታ የሃገሪቱ
ህዝቦች የሚነገሩ የተወሰኑ ቋንቋዎችን በፌዴራል ቋንቋነት መቀበል አስፈላጊ ከመሆኑም
በላይ እነኝህን ቋንቋዎች እንደየሰዉ ምርጫ ለመማር የሚያስችል ሁኔታን በየትኛውም
ክልል ማመቻቸትም ያስፈልጋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ፣ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን
ከማጠናቀቃቸው በፊት፣ ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ቢያንስ አንድ የፌዴራል
ቋንቋን እንዲማሩ ማበረታታት የፌዴራል ሥርዓቱን ማህበራዊ መሰረት በማጠናከር ረገድ
ታላቅ ድርሻ ይኖረዋል። ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን እርምጃዎች በመውሰድ፣ ቋንቋዎቻችን
የግጭቶች ምንጭ ከመሆናቸው ይልቅ የሃገራዊ ልማት እና አንድነት መሳሪያዎቻችን
ልናደርጋቸው እንችላላን። እዚህ ላይ፣ ለረጂም ጊዜ የነበረውን ተቋማዊ አድልኦን ጨምሮ፣
በበርካታ ምክንያቶች የተነሳ መጀመሪያው ላይ አንደኛው ቋንቋ ከሌላው የተሻለ ተቀባይነት
ሊኖረው ይችላል ። ይህን ሁኔታ ግን፣ ሌሎች አስገዳጅ ተቋማዊ ሁኔታዎችን በመጫን
32
ሳይሆን፣ ማናቸውም ተቋማዊ አድሎዎችን በማስወገድ እና በግለሰቦች ፈቃድ ላይ
የተመረኮዘ የቋንቋ ትምህርቶችን በማስፋፋት ማጣጣም ይቻላል።
32 እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በማንኛውም ከአንድ በላይ የፌዴራል ቋንቋ ባላቸው ሃገሮች
የሚያጋጥም እንጂ ለኢትዮጵያ ብቻ የተለየ አይደለም። እንደምሳሌም፣ በእንግሊዝኛ እና
በፈረንሳይኛ መካከል በካናዳ፣በፈረንሳይኛ እና በፍሌሚሽ መካከል በቤልጂየም፣ እንዲሁም
በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ እና በጣሊያንኛ መካከል በስዊዘርላንድ ያለውን ሁኔታ መመልከት
ይቻላል።
83