Page 13 - Ethiopia in the Bible by Abune Petros 2
P. 13
ዶክተር ላጲሶ ብዙ ጠቃሚ ነጥቦችን አንሥተዋል ። የመጀምሪያው በአፍሪካ ቀንድ የኖረና የሚኖረው ሕዝብ በሙሉ
የተፈረጀው ኩሽ በሚለው ስም ብቻ ነው ። ይህ ደግሞ ሌላ አፍሪካዊ ከለር የለም ፣ ሌላ አፍሪካዊ ከለር ካለም ከውጭ
የመጣ ነው የሚል ይሆናል ። ሁለተኛው ነጥብ ይህን ስም የሰጡ ዘረኛ ነጮች በተለይም የጀርመን ሥነ ልሳን አጥኚዎች
ናቸው ። ሦስተኛው ነጥብ የጀርመኖቹ የታሪክ ፍልስፍና የሰው ዘር የተገኘው በመካከለኛው ምሥራቅ ነው ፣ ይህ
በመካከለኛው ምሥራቅ የተገኘው ሰውም ዘሩ የተለየ ነው የሚል የተሳሳተ የታሪክ ግንዛቤ አስጨብጠዋል የሚሉት ዋና
ዋናዎቹ ናቸው ።
ይህን ያደረጉት አሉ ዶክተር ምዕራባውያን ነጭ የታሪክ ምሁራን የኢትዮጵያንና የግብጽን የኑብያን ሥልጣኔ በመካድ
ነው ። ይህም ጥቁር አይሠራም ፥ ሥልጣኔም የለውም ለማለት ያደረጉት ሴራ ነው ። በዚህ ተነሥተው አሉ ዶክተር ላጲሶ
“የግብፅ ፥ የኑቢያ ፥ የኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች መጤዎች ናቸው ብለው አስተማሩ ።
ከዚህ ነጥብ ላይ እንደ ዶክተር በንቲ የሕሊና ቀውስ የመጣው የዶክተር በንቲ አስተማሪዎች የሚያውቁትና
እንዲታወቅ የሚፈልጉትም ይህኑ በዘረኝነት የተመረዘ የዘር ሱስ ፍልስፍና ነው ። የእኛውን ዶክተርም ይህንኑ ግተው
ራሳቸውን እንዳያውቁ ከዚያም ሲያልፍ እንዲጠሉ አድርገው አስተምረዋቸዋል ።
ዶክተር ላጲሶ አቢሲንያ ተብሎ የመጠራት አባዜ የመጣውም ከምን እንደ ሆነ ያብራራሉ ። የመጀመሪያ
የአውሮፓውያን የዘረኝነት መሠረት የተነሣው ጥቁር ሰው አይደለም ከሚል ከንቀት ነው ። ይህም የግሪክ ሥልጣኔ
ከግብጽና ከኑብያ አልመጣም ለማለት ይሞክራል ። ሁኖም የሦስቱ ጥቁር ሕዝብ ሥልጣኔዎች የነሱ የሥልጣኔ ምንጭ
መሆናቸውን አግኝተዋቸዋል ይላል ። ይህ ግኝት አውሮፓውያንን ከአጣብቂኝ ውስጥ ስላገባቸው አንድ ዘዴ መቀየስ
ነበረባቸው ። ይህንም ሲቀጥሉ ዶክተር እንዲህ አሉ ፦
ስለዚህ አውሮፓውያን ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ ፣ በመግባታቸውም ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በመፋቅ
አቢሲኒያ በሚል ስያሜ ተኩት ። የአንድን ነገር ህልውና ለማጥፋት መጀመሪያ መጠሪያውን መቀየር የተለመደ አካሄድ
መሆኑን ካርል ማርክስ በአጽንኦት መግለጹን እዚህ ላይ ማስታወስ ይጠቅማል” በማለት ገልጸውታል ።
ለዚህ ጽሑፍ ከዚህ ሌላ መሄዱ አስፈላጊ አይደለም እንጂ እጅግ ብዙ ማስረጃዎች ማቅረብና መተንተን ይቻላል ።
ዶክተር ላጲሶን የታሪክ ምንጮቻቸውን ፥ የከርሰ ምድር ምርምር ፥ የሥነ ቋንቋ ሥርዐት ፥ የጥንት የምልክት ጽሑፎች ፥
የቅርብ ጊዜ የግሪክ ፥ የላቲን ፥ እንዲሁም የኢትዮጵያ የነገሥታት ዜና መዋዕሎች ፥ የብራና ጽሑፎች እንደ ሆኑ በአግባቡ
ገልጸዋል ። እነዚህ ሁሉ ከላይኛው ግብጽ ጀምሮ እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ የሚሸፍነው መልክዐ ምድር ኢትዮጵያ
የሚባል አገር እንደ ሆነ፣ በዚህ ውስጥ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦችና መንግሥታት የነበሩ ሲሆን ፥ እነዚህ ሁሉ በአንድ
ኢትዮጵያ በሚል መጠሪያ የሚታወቅ መንግሥት እንደ ነበረ አብራርተዋል ።
ከጥንት ጸሐፍያን በአምስተኛው ክፍለ ዘመን (ከክርስቶስ ልደት በፊት) የነበረው ሔሮዶቱስ የተባለው ጸሐፊ
ኢትዮጵያ ስለሚባል አገር ሕዝብና መንግሥት በሰፊው ዘርዝሯል ። The Land mark Herodotus: The
Histories በተሰኘው ባለ ዘጠኝ ቅጽ መጽሐፍ ቅጽ ሦስት ላይ ያለውን እንመልከት ።
ሔሮዶቱስ የብሉይ ኪዳን ተርጓሚዎች የነበሩትን ሰብዐ ሊቃናት በመቶ ዓመት ይቀድማቸዋል ። ይህ ሰው ትረካውን
የሚጀምረው የፐርሽያ ወራሪ ንጉሥ ኢትዮጵያ የሚባል አገር እንዲሰልሉለት በሚልካቸው መልእክተኞቹ ነው ።
የፐርሽያው ጦረኛ ንጉሥ ሰላዮች እንደ አሁኖቹ ሰላዮች ሁሉ ውሸታሞች ነበሩ ። ውሸታቸው ለሚሰልሉት ለኢትዮጵያ
ንጉሥ ስጦታ ይዘን መጥተናል በማለት አታለው እንደ ሆነ ሔሮዶቱስ ይተርካል ። ግን በውሸት የሚደልሉ መሆናቸውን
ኢትዮጵያውያኑ እንደ ደረሱባቸው ዘግቧል ። እነዚህ ሰላዮች ዓሣ በሊዎች ተብለው የተጠቀሱ ሲሆን ፥ ብዙ ስጦታም
ለኢትዮጵያ ንጉሥ አቅርበዋል ። ግን በመጨረሻ ላይ መዋሸታቸው ከዚያው እንዳሉ ታውቆባቸዋል ።
“.ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።” መዝሙረ ዳዊት - ም. 68 ቁ. 31 13